Skip to content Skip to sidebar Skip to footer

ለመጪዎቹ ሁለት ዓመታት በሥራ አመራርነት የሚያገለግሉ የኮሚቴ አባላት ተመረጡ።

ቦስቶን ፡ ህዳር 29,2017 ዓ.ም

ለመጪዎቹ ሁለት ዓመታት መካነ ሕይወት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያንን በሥራ አመራርነት የሚያገለግሉ የኮሚቴ አባላት በጠቅላላው ጉባኤ ተመርጠዋል።

 

የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትን በመምረጥ የተጀመረው 2017 ዓ.ም የስራ አመራር ኮሚቴ ምርጫ እ.ኤ.አ ዲሴምበር 8,2025 በእለተ እሑድ የኮሚቴውን አባላት በመምረጥ ተጠናቋል። በቁጥር ሰባት አባላትን የያዘው ይህ አመራር ኮሚቴ ለቀጣዮቹ ሁለት ተከታታይ አመታት የሚያገለግል ሲሆን ቤተ ክርስቲያኒቷ የጣለችበትን ኅላፊነት እንዲወጣ በተለያዩ አባል ምዕመናን አደራ ተሰቶታል።

የቤተ ክርስቲያናችን የስብከተ ወንጌል ሃላፊ በሆኑት በመጋቢ ሃይማኖት ቀሲስ ኤፍሬም ቃለ እግዚአብሔር የተጀመረው የምርጫ ሂደት በዋና አስተዳዳሪው በሊቀ ካህናት ቆሞስ አባ ሃጎስ ቡራኬ ቀጥሎ የአስመራጭ ኮሚቴ አባላት ምርጫውን በተመለከተ ማብራሪያ በሚፈልጉ ጉዳዮች ዙርያ ሃሳቦችን አንስተው የደረሱባቸውን የምርጫ አካሄድ ውሳኔዎች ለጉባኤው አድርሰዋል።የቀረቡትን ተጠቋሚዎች ለምእመናን በመዘርዘር የቀጠለው መርሃ ግብሩ የተጠቆሙ ነገር ግን የአስመራጭ ኮሚቴው በተከተላቸው የተለያዩ መስፈርቶች ከስራ አመራር ኮሚቴ ምርጫ ውስጥ እንዳይካተቱ የተደረጉትን ምእመናን ከነምክንያታቸው ለጠቅላላ ጉባኤው ያብራሩ ሲሆን ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከምእመናን ለቀረቡለት ጥያቄዎችም ምላሾችን ሰተዋል።

የተጠቆሙትን ምእመናን ለጠቅላላ ጉባኤው ያስተዋወቁት የምርጫ አስፈጻሚ አባላቱ ተጠቋሚዎች እራሳቸውን ለምእመኑ እንዲያሳዩ ያደረጉ ሲሆን ተጠቋሚዎችም ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸውን እና ፍቃዳቸውን በሚያረጋግጥ መልኩ ለጉባኤው ታይተዋል።በቤተክርስቲያኑ የስራ አመራር ምርጫ ታሪክ በአይነቱ ለየት ባለ መልኩ የቀረበውን የምርጫ ሂደት በተመለከተ ለጉባኤው ገለጻ የሰጡት የአስመራጭ ኮሚቴ አባላቱ ጨምረው በወረቀት ታግዞ ሰለሚካሄደው የስራ አመራር ምርጫ ግልጽነት ያለው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በወቅቱ በጉባኤው ያልተገኙ ነገር ግን በድምጽ መስጫ ወረቀቱ ላይ የተካተቱ ምእመናን ከምርጫው አስቀድሞ በሂደቱ እንዳይካተቱ ተደርገዋል።

የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላቱ ለምርጫ መጀመር አስፈላጊ የሚሏቸው ሁኔታዎች መሟላታቸውን እንዳረጋገጡ ምርጫው እንዲጀመር ያስደረጉ ሲሆን የምርጫ ወረቀቶችም ለአባል ምእመናን ታድለዋል።ይህንን የምርጫ ሂደት በቤተ ክርስቲያናችን የተገኙ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት የመጡ ምእመናን በታዛቢነት የተከታተሉት ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ የቤተ ክርስቲያናችን አባቶች የሆኑት አስተዳዳሪያችን ሊቀ ካህናት ቆሞስ አባ ሃጎስ እንዲሁም የስብከተ ወንጌል አላፊው መጋቢ ሃይማኖት ቀሲስ ኤፍሬም ሂደቱ ስርዓቱን ጠብቆ እንዲካሄድ የአባትነት አላፊነታቸውን ተወተዋል።

ለአባል ምእመናን የተሰጡት የምርጫ ወረቀቶች በቀረቡት መስፈርቶች መሰረት መሞላታቸውን በማረጋገጥ የተሰበሰቡ ሲሆን የምርጫው ውጤት ለማሳወቅ እንዲቻል የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በአባቶች እና በምእመኑ ፊት የቆጠራው ሂደት እንዲጀምር አድርገዋል።የቆጠራው ሂደት እየተካኤደ መጋቢ ሃይማኖት ቀሲስ ኤፍሬም ሰፋ ያለ ቃለ እግዚአብሄር ያስተማሩ ሲሆን ጸሎተ ሃይማኖትን በተመለከተ በተነሳ ሃሳብ ዙርያ እጅግ ጠቃሚ ሃሳብ ለጉባኤው አካፍለዋል።

የቆጠራው ሂደት መጠናቀቁን ተከትሎ የአስመራጭ ኮሚቴው በአብላጫው የጉባኤ ተሳታፊ አባላት የተመረጡ ቁጥራቸው ሰባት የሆኑ ያብዛኛውን ምእመን ድምጽ ያገኙ አዳዲስ የስራ አመራር የኮሚቴ አባላት ለጉባኤው የገለጹ ሲሆን ይህንኑ ተከትሎ የተመረጡት አባላት ለጉባኤው እንዲታዩ ተደርጓል።በስራ አመራር ደረጃ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ እዚሁ ሀገር ተወልደው ያደጉ ልጆች በመካተታቸው እና ይሳደጋቸውን ቤተ ክርስቲያን እና ምዕመን ለማገልገል በመመረጣቸው ለዚህም በመብቃታቸው ተስፋው ከምእመኑ ባሻገር በውጪ ሀገራት ለሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በመሆኑ ምሳሌነቱ የጎላ መሆኑን ሀሳባቸውን የሰጡ የጉባኤው ተሳታፊዎች በደስታ ገልፀዋል።የምርጫውን ሂደት አካሄድ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ አንዳንድ ምእመናን ሃሳባቸውን ያካፈሉ ሲሆን በመጨረሻም የቤተ ክርስቲያናችን ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት ሊቀ ካህናት ቆሞስ አባ ሃጎስ የማሳረጊያ ጸሎተ ቡራኬ በመስጠት ጉባኤው በታቀደለት ጊዜ በእግዚአብሔር መልካም ፍቃድ እና ቸርነት በጥሩ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ሆኗል።