Skip to content Skip to sidebar Skip to footer

መካነ ህይወት ቅዱስ ሚካኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን

መካነ ሕይወት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን

የመካነ ሕይወት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በሰሜን አሜሪካ በቦስተን ማሳቹሴትስ የሚገኝ አንጋፋና ቀደምት ቤተ ክርስቲያን ነው።ቤተ ክርስቲያኑ ላለፉት አስርት ዓመታት በቦስተን እና አካባቢው መኖሪያቸውን ላደረጉ ምእመናን ሁሉን አቀፍ መንፈሳዊ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል። በአምላካችን መልካም ፍቃድ የራሱ የሆነ ህንጻ ቤተ ክርስቲያን በመግዛት አገልግሎቱን እየሰጠ የቀጠለው ቤተ ክርስቲያኑ ይህንኑ የዘወትር መንፈሳዊ አገልግሎት ለመላው ቦስተን እና አካባቢው ምእመን ከመቼውም ጊዜ በላይ አጠናክሮ ቀጥሏል።

በሰሜን አሜሪካ ተወልደው ያደጉ ህፃናት-ልጆችን ከልጅነታቸው ጀምሮ በመረከብ መንፈሳዊ ምግብ በመመገብ የቤተ ክርስቲያናችን የቅዳሴ ስርዓት ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማስቻል በከተማችን የመጀመሪያውን የድቁና ማዕረግ የሰጠ ቤተ ክርስቲያን ነው።

ወጣቶቹ ለዚህ ታላቅ መንፈሳዊ ክብር እንዲበቁ ተከታታይነት ያለው መንፈሳዊ ትምህርት በማስተማር እና ለአገልግሎቱም የሚያበቃውን ተገቢ ዝግጅት እንዲያደርጉ እንደ አምላካችን ቅዱስ ፈቃድ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል።የቤተ ክርስቲያናችን ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት ሊቀ ካህናት ቆሞስ አባ ሃጎስ ይህንን መሰል አዲስ ጅማሮ በማስጀመሩ በኩል ሊጠቀስ የሚችል ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። አባታችን ቤተ ክርስቲያኑ ሲጀምር ከነበረበት ጊዜ አንስተው አሁን እስካለበት ህንጻ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ላለፉት 30 አመታት ከቤተ ክርስቲያኑ ጋር በጥንካሬ የቆዩ መላው የቦስተን እና አካባቢው ምእመን የሚወዳቸው እና የተከበሩ አባት ናቸው።

 

የመካነ ሕይወት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ከመንፈሳዊ አገልግሎት ጎን ለጎን ወጣቶች በአለማዊ ህይወታቸው በፈሪሃ እግዚአብሔር ጥላ ስር ሆነው እንዲያድጉ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን በቤተ ክርስቲያኑ ስር ባለው አንቀጸ ተዋህዶ ሰንበት ት/ቤት በኩል በርካታ ስራዎችን በሁሉም እድሜ ክልል ላሉ ህጻናት እና ወጣቶች እየሰጠ ይገኛል።

የቤተ ክርስቲያኑ መንፈሳዊ አገልግሎት ቅዱስ ሲኖዶስ ያስቀመጠለትን የቤተ ክርስቲያን ዶግማ፣ቀኖና፣ትዕውፊት እና ሥርዓት በተገቢው ሁኔታ ለማስኬድ እንዲያስችል በድጋፍ ሰጪነት የተቋቋሙ ሶስት ዋና ዋና ኮሚቴዎች አሉት።እነሱም በየሁለት አመት የሚመረጥ የስራ አመራር ኮሚቴ ፣ በየሶስት አመቱ የሚመረጥ የሰበካ ጉባኤ እንዲሁም ተጠሪነቱ ለጠቅላላው ጉባኤ የሆነ የኦዲት አገልግሎት ኮሚቴ ናቸው። ቤተ ክርስቲያኒቷ ተተኪና ተረካቢ ትውልድ ለማዘጋጀት በማሰብ የቤተ ክርስቲያኑ ምእመናን እዚሁ ሀገር ተወልደው ያደጉ ልጆች እድሜያቸው ከፍ ሲል በቤተ ክርስቲያኑ አስተዳደር ውስጥ ተካተው እንዲያገለግሉ በማድረግ ሂደት ላይ ከፍተኛውን ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።

የመካነ ህይወት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በቦስተን እና አካባቢው ለሚገኘው ለመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነተ ተከታይ ለረጅም አመታት ሲሰጥ የቆየውን መንፈሳዊ አገልግሎት በማጠናከር የሚቀጥል ሲሆን በቦስተን እና አካባቢው የሚገኙ ምእመናን ዘወትር እሁድ ለቅዳሴ እንዲሁም ለተለያዩ አመታዊ በዓላት በቤተ ክርስቲያናችን በመገኘት በአንድነት አምላካችን ልዑል እግዚአብሔርን በህብረት እንድናመልክ ቤተ ክርስቲያናችንንም እንዲጎበኙ መንፈሳዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን። ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ቤት የሆነ የሁላችን በመሆኑ ማንኛውም አይነት መንፈሳዊ አገልግሎት ለማግኘት የቤተ ክርስቲያኑን የመንፈሳዊ አገልግሎት ክፍል ማግኘት ይችላሉ።

የእግዚአብሔር ቸርነት የቅዱስ ሚካኤል ረድኤት እና በረከት ከእርስዎ እና ከመላው ቤተሰብዎ ጋር ይሁን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ወወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር

አሜን