ኢትዮጵያ ክርስትናን የተቀበለችው በመጀመሪያው ምዕት ዓመት ይሁን እንጂ በሲኖዶስ ሕግ የኤጲስ ቆጶስ መንበር የተሰጣት በአራተኛው ምዕት ዓመት በ330 ዓ.ም. ነው፡፡
ኦርቶዶክስ የተሰኘው ቃል ከሁለት የግሪክ ቃላት ተገናኝቶ አንድ የሆነ ቃል ነው። /ኦርቶ/ ርቱዕ፣ የቀና /ዶክሳ/ሃይማኖት ማለት ሲሆን ኦርቶዶክስ የቀና ቀጥ ያለ ሃይማኖት ማለት ነው።በግእዝ ልሳን /ርትዕት ሃይማኖቶሙ ለዱሳን አበዊነ/ የአባቶቻችን ሃይማኖት የቀናች ቀጥ ያለች ናት የሚል ቃል በቅዱሳት መጻሕፍት ይነበባል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሠረተ እምነትዋን የምትገልጥባቸውና የምታስተምርባቸው አምስት አዕማደ ምሥጢር አሏት፡፡ አዕማድ ማለትም ምሰሶዎች ማለት ነው፡፡
የምሥጢረ ምሰሶችም የተባሉበት ምክንያት ቤት በምሰሶ ተደገፎ እንደሚጸና ምእመናንን በትምህርተ ሃይማኖት ደግፈው የሚያጸኑ ስለሆነ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰባት ዐበይት ምሥጢራት ምእመናን ታገለግላለች፤ ምሥጢራት የተባሉበትም ምክንያት በዓይናችን ልናያቸው በእጃችን ልንዳስሳቸው የማንችል ልዩ ልዩ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታወዎች በእነዚሁ ምሥጢራት አማካይነት የሚሰጡን ስለሆነ ነው፡፡