አምስቱ አዕማደ ምሥጢር
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሠረተ እምነትዋን የምትገልጥባቸውና የምታስተምርባቸው አምስት አዕማደ ምሥጢር አሏት፡፡ አዕማድ ማለትም ምሰሶዎች ማለት ነው፡፡ የምሥጢረ ምሰሶችም የተባሉበት ምክንያት ቤት በምሰሶ ተደገፎ እንደሚጸና ምእመናንን በትምህርተ ሃይማኖት ደግፈው የሚያጸኑ ስለሆነ ነው፡፡ እነዚህም አምስቱ አዕማደ ምሥጢር መጽሐፋዊ መሠረት ያላቸው ናቸው፡፡ (1ቆሮ.14፥19)፡፡ በዚህም መሠረት አምስቱ አዕማደ ምሥጢር የእምነታችን መግለጫ በሆነው በጸሎተ ሃይማኖት ተዘርዝረው ይተረጐማሉ፡፡
- ምሥጢረ ሥላሴ
ይህ ክፍል የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት የሚገለትበተ የምሥጢር ዓምድ ነው፡፡ ሥላሴ በስም፣ በግብር፣ በአካል ሦስት ሲሆኑ በባሕርይ፣ በመለኮት፣ በህልውና በፈቃድ አንድ ናቸው፡፡
የስም ሦስትነት፡- አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ
የግብር ሦስትነት፡- አብ ወላዲ፣ ወልድ ተወላዲ፣ መንፈስ ቅዱስ ሠራፂ ነው፡፡
የአካል ሦስትነት፡- ለአብ ፍጹም አካል አለው፣ ለወልድ ፍጹም አካል አለው፣ ለመንፈስ ቅዱስ ፍጹም አካል አለው፡፡
አብ ልብ ነው፣ ወልድ ቃል ነው፣ መንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ ነው፡፡ አብ ለራሱ ለባዊ ሆኖ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ልባቸው ነው፡፡ ወልድ ለራሱ ቃል ሆኖ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለራሱ እስትንፋስ (ሕይወት) ሆኖ ለአብና ለወልድ እስትንፋስ (ሕይወት) ነው፡፡
ሥላሴ በስም፣ በግብር፣ በአካል ሦስት ናቸው ብንልም በባሕርይ፣ በመለኮት፣ በህልውና እና በፈቃድ አንድ ስለሆኑ አንድ አምላክ እንጂ ሦስት አማልክት አይባሉም፡፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በየአካላቸው ሲኖሩ ህልውናቸው አንዲት ናት፡፡ (አቡ ሊዲስ ሃይ.አበው ምዕ. 40 ክፍ. 4 ቁ 6)፡፡
የሥላሴ የሦስትነት ስማቸው የአንዱ ወደ አንዱ አይፋለስም፡፡ ይህም ማለት የአብ ስም ተለውጦ ወልድ መንፈስ ቅዱስ፣ የወልድ ስም ተለውጦ አብ መንፈስ ቅዱስ፣ የመንፈስ ቅዱስ ስም ተለውጦ አብ ወልድ ተብሎ አይጠራም፡፡ አብ አብ ነው፡፡ ወልድ ወልድ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ሦስቱም በየስማቸውና በየአካላቸው ጸንተው (አግናጢዎስ ሰማዕት ሃይ.አበው ምዕ.11 ክፍል 1 ቁጥር 7-8)፡፡
በአንድነት ስማቸው ግን እግዚአብሔር፣ አምላክ በመባል ሦስቱም ይጠሩበታል፡፡ እግዚአብሔር አብ፣ እግዚአብሔር ወልድ፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ፣ አንድ እግዚአብሔር፡፡ አብ አምላክ፣ ወልድ አምላክ፣ መንፈስ ቅዱስ አምላክ፣ አንድ አምላክ ይባላል፡፡ ይህንም ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ሊቃውንት በሃይማኖተ አበው ሲያስረዱ “በእግዚአብሔር አብ፣ በእግዚአብሔር ወልድ፣ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እናምናለን” ብለዋል (ሃይ. አበው ዘሠለስቱ ምእት ምዕ.19 ክፍል 1 ቁጥር 30)፡፡
የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አትናቴዎስ “አብ አምላክ ነው፣ ወልድ አምላክ ነው፣ መንፈስ ቅዱስ አምላክ ነው፤ ግን አንድ አምላክ እንጂ ሦስት አማልክት አይባሉም” በማለት ገልጾአል (ሐዋርያዊ አትናቴዎስ ሃይ. አበው ምዕ.24 ክፍል 4 ቁጥር 4)፡፡ ስለ ሥላሴ አንድነትና ሦስትነት በብሉይና በሐዲስ ኪዳነናት በብዙ ቦታ ተገልጾአል፡፡
- በብሉይ ኪዳን ዘፍ.1፥26፣ 2፥18፣ 3፥22፣ 11፥7፣ 18፥1-8፤ መዝ.33፥6፣ 146፥5፤ ኢሳ.6፥3፣8፡፡
- በሐዲስ ኪዳን ማቴ.3፥16-17፣ 28፥19፤ ዮሐ.14፥26፣ 2ቆሮ.14፥13፤ 1ጴጥ.1፥2፤ 1ዮሐ.5፥7-8፡፡
- ምሥጢረ ሥጋዌ
ምሥጢረ ሥጋዌ ከሦስቱ አካላት አንዱ እግዚአብሔር ወልድ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍስዋም ነፍስ ነሥቶ በሥጋ የመገለጹ፣ አምላክ ሰው ሰወው አምላክ የመሆኑ ምሥጢር ነው፡፡ “ቃል ሥጋ ሆነ በእኛም አደረ” (ዮሐ.1፥14)፡፡
እግዚአብሔር ወልድ ሰው የሆነበት ምክንያት
እግዚአብሔር የመጀመሪያዎቹን ሰዎች አዳምንና ሔዋንን በንጹሕ ባሕርይ ያለ ሞት ፈጥሮአቸዋል፡፡ “እግዚአብሔር ሞትን አልፈጠረም” (መጽ. ጥበብ 1፥13)፡፡ ይሁን እንጂ የሰው ልጅ የተሰጠውን ትእዛዝ በማፍረስ ስለ በደለ ሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ፣ ርደተ መቃብርና ገሃነም ተፈረደበት (ዘፍ.3፥19-24)፡፡ እግዚአብሔር ሞትን አልፈጠረምና ነዋሪ ይሆን ዘንድ ፍጥረትን ፈጥሮዋል እንጂ የሰዎች ጥፋት ደስ አያሰኘውም፤ በእጃችሁ ሥራ ሞትን አታምጡ፡፡ የሰውም መፈጠር ለደኅንነት ነውና፡፡ በእነርሱ ዘንድ ሁሉን የሚያጠፋ መርዝ ኃጢአት አልነበረምና፡፡
ሕይወት የማታልፍ ስለሆነች ለመቃብርም በዚህ ዓለም ግዛት አልነበረውምና እግዚአብሔርን የዘነጉ ሰዎች ግን በቃል ጠሩት፡፡ ባልንጀራም አደረጉት በዚሁም ጠፉ፡፡ (ጥበብ 1፥12-16፣ ሮሜ 6፥23)፡፡ “እግዚአብሔር ለሞት አልሠራንምና ለሕይወት እንጂ” (1ተሰ.5፥9)፡፡
አዳምና ሔዋን በበደላቸው ከክብራቸው ተዋረዱ፤ ከጸጋቸው ተራቆቱ፤ ከተድላ ገነት ወጡ፤ ተባረሩ፤ በሥራቸው በራሳቸው ላይ ብዙ መከራን አመጡ፡፡ ተጨነቁ፣ ተቸገሩ፣ ለአጋንንትም ተገዦች ሆኑ፡፡ በኃጢአት ምክንያት ወደ ዓለም የገባው ሞት በሰው ላይ ሠለጠነ፤ ከአዳም እስከ ክርስቶስ ሞት ነገሠ፣ ኃጢአት ባልሠሩትም ጭምር፡፡ (ሮሜ.5፥12-14)፡፡
ይህ ሁሉ መከራ የመጣባቸው ሕገ እግዚአብሔርን በመተላለፋቸው መሆኑን አውቀው ተጸጸቱ፤ አዘኑ፤ አለቀሱ፤ ንስሐ ገብተው ፈጣሪያቸውን ለመኑት፡፡ እግዚአብሔርም በፈታሒነቱ አንጻር መሐሪነቱ አለና የአዳምነና የሔዋንን ንስሐቸውን ተቀብሎ ኀዘናቸውንና ለቅሶአቸውን ተመልክቶ ሊያድናቸው ወደደ፤ ተስፋም ሰጣቸው (ኢሳ.63፥8፣ ዕብ.2፥14-16)፡፡
ይህም የተሰጠው ተስፋ የሚፈጸምበት ዘመን በደረሰ ጊዜ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለlም ሕይወት እንዲያገኝ ልዑል እግዚአብሔር ተቀዳሚ ተከታይ የሌለውን አንድያ የባሕርይ ልጁን ወደ ዓለም ላከው፤ እግዚአብሔር ወልድም ከሰማየ ሰማያት ንጽሕት ከምትሆን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው ሆኖ ተወለደ፡፡ ሰው ሆነ ማለትም በተለየ አካሉ ነፍስና ሥጋን ተዋሐደ ማለት ነው፡፡ በዚህም የነቢያት ቃል ተፈጻመ፡፡ (ኢሳ.7፥14፣ 9፥6፣ ሚክ.5፥2፣ ገላ.4፥4)፡፡
መለኮት ከሥጋ፣ ሥጋ ከመለኮት ጋራ ያለ መለወጥ፣ ያለ መቀላቀል፣ ያለ መለያየትና ያለ መከፈል በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆነ፡፡ ሰው ከመሆኑ አስቀድሞ ሰውም ከሆነ በኋላ አንድ ወልድ አንድ ክርስቶስ ነው፡፡ (ቄርሎስ ሃይ.አበው ምዕ.78 ክፍል 48 ቁጥር 9-18)፡፡ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙም “በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ አምላክም የሆነ ሰው እርሱ ብቻ ነው” (ሃይ.አበው ምዕ.61 ክፍል 4 ቁጥር 23)፡፡ ሥጋም በተዋሕዶተ ቃል እንደከበረ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “በሥጋ የነበረ ንዴት በተዋሕዶተ ቃል ጠፋ፤ የቃል ክብር ለሥጋ በተዋሕዶ ገንዘቡ ሆነ” ብሎአል (ዮሐ.አፈ. ሃይ.አበው ምዕ. 66 ክፍል 9 ቁጥር 18-19)፡፡
ከተወለደም በኋላ ከኃጢአት በቀር ሰው የሚሠራውን ሥራ ሁሉ እየሠራ አደገ፤ በዚህም ዓለም 33 ዓመት ከ 3 ወር ኑሮና አስተምሮ ስለእኛ የሞት ፍርድን ተቀበለ በመስቀል ተሰቅሎ ሞተ፤ በሞቱም ሞትን አጠፋ፤ ዓለምን አዳነ፤ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር አድሮ ተነሣ፡፡ ከተነሣም በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ እየታየ ጉባኤ ሠርቶ መጽሐፈ ኪዳንን እያስተማረ በምድር ላይ አርባ ቀን ቆየ፡፡ በአርባኛውም ቀን ደቀመዛሙርቱ እያዩት በመላእክት ምስጋናና በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ በአባባም ቀኝ ተቀመጠ፤ ዳግመኛም በሕያዋንና በሙታን ላይ ሊፈርድና ለሁሉም እንደሥራው ዋጋውን ይከፍል በዘንድ ይመጣል፡፡ (ዮሐ.3፥13፣ 1ጴጥ.3፥22፣ ማቴ.25፥31፣ ኤፌ.4፥8-10፣ የሐዋ.ሥራ 2፥30፣ 2ቆሮ.5፥14)፡፡
ስለዚህ በምሥጢረ ሥጋዌ የሚገለጠው ትምህርተ ክርስቶስን ቃለ አብ ወመንፈስ ቅዱስ፣ ድንግል ማርያምን በአማን ወላዲተ አምላክ ወላዲተ ቃል ብሎ ማመን ነው፡፡ (ቄርሎስ ሃይ አበው)፡፡
- ምሥጢረ ጥምቀት
ጥምቀት በምሥጢረ ሥላሴና በምሥጢረ ሥጋዌ ለሚያምን ሰው ሁሉ የሚሰጥ የኃጢአት መደምሰሻ፣ ከአግዚአብሔር የልጅነትን ጸጋ መቀበያ፣ የመንግሥተ ሰማያት መውረሻ ነው፡፡ ምሥጢር መባሉም ካህኑ ለጥምቀት የተመደበውን ጸሎት አድርሶ ሲባርከው ውሃው ተለውጦ ማየ ገቦ ስለሚሆንና ከእግዚአብሔር ዘንድ የጸጋ ልጅነትን ስለሚያሰጥ ነው፡፡ (ዮሐ.19፥34-35)፡፡
አምኖ የሚጠመቅ ሁሉ የኃጢአት ሥርየትን ያገኛል፤ “ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኃጢአት – ኃጢአትን ለማስተስረይ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን” (ጸሎተ ሃይማኖት)፡፡ ማንም ሰው በጥምቀት ከእግዚአብሔር ይወለዳል፤ ከፍዳ ይድናል፡፡ “ያመነ የተጠመቀም ይድናል፤ ያላመነና ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል” (ማር.16፥16፤ የሐዋ.2፥28)፡፡ ከሥላሴ መወለድም የእግዚአብሔርን ርስት መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ነው፡፡ መንግስተ ሰማያት በጥምቀት እንጂ ያለ ትምቀት ልንገባባት እንደማንችል ጌታችን አስተምሮናል፡፡ “እውነት እውነት እልሃለሁ ማንም ከውሃ እና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት አይችልም” (ዮሐ.3፥5፣ ቲቶ.3፥4-7)፡፡
ስለ ጥምቀት በሕግና በነቢያት የተነገሩ ትንቢቶችና ምሳሌዎች አሉ፡፡
ሀ. ትንቢት፡- “የጠራ ውሃ እረጫችኋለሁ ትጠሩማላችሁ”፤ “ከርኵሰታችሁም ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አነጻችኋለሁ” (ሕዝ.36፥25፣ ሚክ.7፥19)፡፡
ለ.ምሳሌ፡-
- ግዝረት
ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ ሆኖ በብሉይ ኪዳን ሲሠራበት ኖሮአል፡፡ ግዝረት ለአብርሃም የቃል ኪዳኑ ምልክት ሆኖ በመሰጠቱ በስምንተኛው ቀን ያልተገረዘ ሁሉ ከአብርሃም ቤተሰብ አይቈጠርም ምድረ ርስትን አይወርስም፤ ከተስፋው አይካፈልም፡፡ የእግዚአብሔርም ወገን አይባልም ነበር፡፡ (ዘፍ.17፥7)፡፡
በሐዲስ ኪዳን በግዝረት ፈንታ ጥምቀት ተተክቶአል፡፡ ያልተጠመቀ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅ አይባልም፤ መንግሥተ ሰማያትን አይወርስም፡፡ (ቈላስይስ 2፥11)፡፡
- የኖኅ መርከብና የእስራኤል ቀይ ባሕርን መሻገር
የጥምቀት ምሳሌዎች ነበሩ (1ጴጥ.3፥19፣ 1ቆሮ.10፥2)፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንቢቱን ለመፈጸም፣ ምሳሌውን አማናዊ ለማድረግ በማየ ዮርዳኖስ በዮሐንስ እጅ ተጠምቆአል፡፡ (ማቴ.3፥16፤ ማር.1፥9፤ ሉቃ.3፥21፣ ዮሐ.1፥31)፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምሥጢረ ጥምቀትን ለወንዶች በ40 ቀን፣ ለሴቶች በ80 ቀን ትፈጽማለች፡፡ ይህም ዕድሜ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ከእግዚአብሔር ልጅነትን የተቀበሉበት ነው፡፡ (ኩፋሌ 4፥2-15)፡፡
- ምሥጢረ ቁርባን
ቅዱስ ቁርባን ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት፣ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ የምንሆንበት ምሥጢር ነው፡፡ “እውነት እውነት እላችኋለሁ የወልደ እጓለ እመሕያው ክርስቶስን ሥጋውን ካልበላችሁ ደሙን ካልጠጣችሁ የዘላለም ሕወት የላችሁም፡፡ ሥጋዬን የበላ ደሜን የጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፡፡ ሥጋዬና ደሜ ሕይወትነት ያለው እውነተኛ ምግብ ነውና፡፡ ሥጋን የበላ ደሜን የጠጣ ከእኔ ጋር ይነራል፡፡ እኔም ከአርሱ ጋር እኖራለሁ፡፡” (ዮሐ.6፥53-57) ተብሎ ተጽፎአልና፡፡
ስለ ምሥጢረ ቁርባን አስቀድሞ የተነገሩ ትንቢቶችና የተገለጡ ምሳሌዎች አሉ፡፡
ትንቢት
“ከስንዴ ፍሬና ከዌን ከዘይትም ይልቅ በዛ” (መዝ.4፥7)፡፡ “ጥበብ ቤትዋን ሠራች፣ ሰባቱንም ምሰሶዎችዋን አቆመች፣ ፍሪዳዋን አረደች፣ የዌን ጠጅዋንም ደባለቀች፣ ማዕዷንም አዘጋጀች” (ምሳሌ.9፥1-3)፡፡ “የሰው የሕይወቱ መጀመሪያ እህልና ውሃ ዌንና ስንዴ ነው፡፡ (ሲራክ 39፥26)፡:፡ እነዚህም ትንቢቶች በመስቀል ላይ የተሠዋው በግዐ ፋሲካ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋውን ደሙን በስንዴ ኅብስትና በወይን እንደሚሰጥ የተነገሩ ናቸው፡፡
ምሳሌ
የእስራኤል ልጆች ከግብጽ የባርነት አገዛዝ በወጡበት ጊዜ አርደው ሥጋውን እንዲበሉት ደሙንም የቤታቸውን መቃን ጉበነንና መድረኩን ረጭተው ከመቅሠፍትና ከሞተ በኵር እንዲድኑ የተሰጠው የፋሲካቸው በግ በመስቀል ላይ የተሠዋውና ሥጋውንና ደሙን ለሰው ልጆች ሕይወት ቤዛ አድርጎ የሰጠው የወልደ እግዚአብሔር የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ “እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” (ዮሐ.1፥29) ተብሎ በተጻፈው ታውቋል፡፡
ለወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ መምሳሌ የሆነው ካህን መልከ ጼዴቅም በኅብስትና በወይን ያስታኩት ነበር፡፡ (ዘፍ.14፥18)፡፡ እነዚህን ትንቢቶች ምሳሌዎች ለመፈጸምና አማናዊ ለማድረግ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሴተ ሐሙስ በተዘጋጀው የፋሲካ ዕራት ኅብስቱን አንስቶ አመስግኖ ባርኮ ቆርሶ ለደቀ መዛሙርቱ “ይህ ሥጋዬ ነው፣ እንኩ ብሉ” ብሎ ሰጣቸው፤ ጽዋውንም አንሥቶ አመስግኖ ባርኮ “እንኩ ሁላችሁ ከዚህ ጠጡ፣ ለሐዲስ ኪዳን ኃጢአትን ለማስተስረይ ስለ ብዙ ሰዎች የሚፈስ ደሜ ይህ ነው” ብሎ ሰጣቸው (ማቴ.26፥28፣ ማር.14፥22፣ ሉቃ. 22፥19)፡፡
ይህ ምሥጢር አሁንም በቤተ ክርስቲያናችን ይፈጸማል፡፡ ቄሱ በቅዳሴ ጊዜ ኅብስቱን በፃሕል ወይኑን በጽዋዕ አድርጎ እየባረከ ጸሎተ ቅዳሴውን ሲያደርስበት ኅብስቱ ተለውጦ አማናዊ ሥጋ ወልደ እግዚአብሔር፣ ወይኑ ተለውጦ አማናዊ ደመ ወልደ እግዚአብሔር ይሆናል፡፡
ይህንም ሊቁ ቅዱስ አትናቴዎስ “ካህኑ፡- ሳይባርከውና ሳያከብረው ኅብስትና ወይን እንደሆነ ካህኑ በባረከውና ባከበረው ጊዜ ግን ኅብስቱ ከኅብስትነት የአምላክ ሥጋ ወደ መሆን፣ ወይኑም ከወይንነት የወልደ እግዚአብሔር ደም ወደ መሆን እንደሚለወጥ እናምናለን” ብሎአል፡፡ (አትናቴዎስ ሃይ.አበው ምዕ.28 ክፍ.14 ቁ.22)፡፡
- ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን
ትንሣኤ ሙታን ማለት ከአዳም እስከ ምጽአተ ክርስቶስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩና የሚለዩ የሰው ልጆች ሁሉ በነፍስና በሥጋ አዲስ ሕይወት ለብሰው የሚነሡበት ምሥጢር ነው፡፡
ሰው ሁሉ በሚሞትበት ጊዜ የጻድቅም ሆነ የኃጥእ ሥጋው በመቃብር ይቆያል፡፡ የጻድቃን ነፍስ በገነት፣ የኃጥአን ነፍስ በሲኦል ትቆያለች፡፡ (ሉቃ.16፥19-31)፡፡
የዚህ ዓለም ፍጻሜ ሲደርስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ በሚመጣበት ጊዜ የሰው ልጆች ሁሉ ይነሣሉ፡፡ “ስለዚህ ነገር አታድንቁ በመቃብር ያሉት ሙታን ሁሉ ቃሉን የሚሰሙባት ሰዓት ትመጣለች፤ ሕጉን የፈጸሙ በሕይወት ለመኖር ይነሣሉ፡፡ ክፉ ሥራን የሠሩት ግን በፍዳና በጨለማ ለመኖር ይነሣሉ፡፡” (ዮሐ.5፥28)፡፡
ስለ ትንሣኤ ሙታን ከብሉይ እና ከአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ብዙ ምንባቦች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ በዘዳግም 32፥39፣ “እኔ እገድላለሁ፣ አድንማለሁ” የሚለው ቃል የትንሣኤን ተስፋ ያሳያል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ይላል፡- “ሙታን ይነሣሉ፤ በመቃብር ያሉ ሕያዋን ይሆናሉ፡፡ በምድር ውስጥ ያሉም ደስ ይላቸዋል፡፡ ከአንተ የሚገኝ ጠል ሕይወታቸው ነውና፡፡” (ኢሳ.26፥19-20)፡፡ ነቢዩ ዳንኤልም እንዲህ ሲል ጽፏል፡- “በዚያም በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ እያንዳንዱ ይድናል፡፡ በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉት ብዙዎቹ ይነቃሉ፤ እኩሌቶቸቹ ወደ ዘላለም ሕይወት እከሌቶቹም ወደ ዘላለም ዕፍረትና ወደ ዘላለም ጉስቁልና ይሄዳሉ” (ዳን.12፥1-3)፡፡ ኢዮብም እንዲህ አለ፡- “እኔን ግን የሚቤዠኝ ሕያው እንደሆነ በመጨረሻም ዘመን በምድር ላይ እንዲቆም አውቃለሁ፡፡ እኔ ራሴ አየዋለሁ ይኖቼም ይመለከቱታል” (ኢዮ.19፥25-27)፡፡
የትንሣኤ ሙታን ትምህርት በቃል ብቻ የተነገረ አይደለም፡፡ ከሟቾቹ መካከል ብዙዎቹ ከመቃብር ወጥተው በአደባባይ ሲታዩ በተግባር ተረጋግጧል፡፡ ነቢዩ ኤልያስ እና ደቀ መዝሙሩ ኤልሳዕ ሙታንን አስነሥተዋል፡፡ (1ነገ.17፥21፣ 2ነገ.13፥21)፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በዚህ ዓለም በሚያስተምርበት ጊዜ ሙታንን አስነሥቶአል፡፡ (ማቴ.9፥25፤ ሉቃ.7፥15፣ ዮሐ. 11፥14)፡፡ በተመሳሳይ ሐዋርያት በትምህርታቸው ጊዜ አስነሥተዋል፡፡ ጌታችን በተሰቀለበት ዕለት ከእግረ መስቀሉ ብዙዎች ሙታን ተነሥተዋል፡፡ (ማቴ. 27፥52)፡፡
ይህ ሁሉ የሚያመለክተው የሰው ልጅ በመቃብር ውስጥ ፈርሶና በስብሶ እንደማይቀርና በመጨረሻ ቀን እንደሚነሣ ነው፡፡ ለትንሣኤያችን መሠረት የምናደርገው ግን የክርስቶስን ነው፡፡ “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ እንደተነሣ እኛንም በሐዲስ ትንሣኤ እንደሚያስነሣን እናውቃለን” (2ቆሮ.4፥14)፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አሞንዮስና አውሳብዮስም “ክርስቶስ የሥጋችንን መነሣት ያስረዳን ዘንድ ተነሣ” ብለዋል (መቅድመ ወንጌል)፡፡
ትንሣኤ ለሰው ዘር ሁሉ ነው፤ ጻድቃንም ኃጥአንም ይነሣሉ፡፡ የመጨረሻው የሙታን ትንሣኤ የሚሆነውም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማሳለፍ በሚመጣበት ጊዜ ነው፡፡
በዘመኑ መጨረሻ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሙታንና በሕያዋን ይፈርድ ዘንድ በክብሩና በጌትነቱ ይመጣል፡፡ (መዝ.50፥2፣ ማቴ.25፥31-32፤ ራእ.1፥7)፡፡ አስቀድሞም መላእክትን ይልካቸዋል፡፡ እነርሱም የመለከት ድምፅ ያሰማሉ፤ ሙታንም ይነሣሉ፤ ምድርም አደራዋን ታስረክባለች፡፡
ከዚህ በኋላ ጻድቃንን በቀኙ፣ ኃጥአንን በግራው ያቆማቸዋል፤ ያን ጊዜ ጻድቃን በበጎ ምግበራቸው ይመሰገናሉ፤ ኃጥአን በክፉ ምግባራቸው ይወቀሳሉ፡፡ ጻድቃን ከፀሐይ ሰባት እጅ አብርተው፣ አምላካቸው ክርስቶስን መስለው መንግሥቱን ይይርሳሉ፡፡ ኃጥአን ግን ጠቁረው ጨለማ ለብሰው ለዲያብሎስና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀው ወደ ዘላለም ኩነኔ ይሄዳሉ (ማቴ.13፥42-49፤ 25፥31-43፤ 2ቆሮ. 5፥10፤ ራእ.20፡12)፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ሃይማኖትን ለምእመናን የምታስተምረው ከዚህ በላይ በአምስት ተከፍለው በተገለጡት አዕማደ ምሥጢር መሠረትነት ነው፡፡
ምንጭ፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት፣ የአምልኮ ሥርዓት እና የውጭ ግንኙነት