ስድስቱ እህት የኦርየንታል ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ኦርቶዶክስ የተሰኘው ቃል ከሁለት የግሪክ ቃላት ተገናኝቶ አንድ የሆነ ቃል ነው። /ኦርቶ/ ርቱዕ፣ የቀና /ዶክሳ/
ሃይማኖት ማለት ሲሆን ኦርቶዶክስ የቀና ቀጥ ያለ ሃይማኖት ማለት ነው።በግእዝ ልሳን /ርትዕት ሃይማኖቶሙ ለዱሳን አበዊነ/ የአባቶቻችን ሃይማኖት የቀናች ቀጥ ያለች ናት የሚል ቃል በቅዱሳት መጻሕፍት ይነበባል። በዚህ ስያሜ በምስጢረ ሃይማኖት ትርጉምና በይዘቱ በመለያየት ከሁለት የተከፈሉ አብያተ ክርስቲያን ይጠቀሙበታል። እነርሱም የኦርየንታል አብያተ ክርስቲያንና የግሪክ ቤተ ክርስቲያን የሚከተሉ የምስራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያን ናቸው።የኦርየንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያን ከምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያን የሚለዩት የኦርየንታል ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያን በመባል ነው።
እነዚህም።
-
-
-
-
-
-
-
-
-
- የኢትዮጵያ እና ኤርትራ
- የግብጽ
- የሶርያ
- የአርመን
- የሕንድ ናቸው።
-
-
-
-
-
-
-
-
1. የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ የገባው ቀደም ብሎ በዘመነ ሐዋርያት ታላቅ ባለሥልጣን በነበረው በሕጽዋ ለሕንደኬ ንግሥተ ኢትዮጵያ አማካይነት ነበር። (ሐ.ሥራ 8:26-40) በአራተኛው መቶ ዓመት ከልደተ ክርስቶስ በሗላ በሲኖዶስ ደረጃ ከፍ ብሎ ፍሬምናጦስ የተባለው አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ተብሎ በእስክንድርያው ጳጳስ ሆኖ ተሾመ። እርሱም ብዙዎች ቅድሳት መጻሕፍትን ከሌሎች ልሳናት ወደ ግዕዝ ቋንቋ ተርጉሟል።
በአምስተኛው መቶ ዓመት በሗላ የኬልቄዶንን ጉባኤ የተቃወሙ ዘጠኝ ቅዱሳን መነኮሳት ከባዛንታይን በስደት ወደ ኢትዮጵያ መጡ።ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የመረጡትም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የኬልቄዶንን ጉባኤ ከተቃወሙት መካከል አንዷ በመሆኗ ነበር። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በስድስተኛው እና ሰባተኛው መቶ ዓመታት የሃይማኖት ሥነ ጽሑፍን በእጅጉ አስፋፍታ ነበር።ነገር ግን በሰባተኛው ምእት አመት በቀይ ባሕር አካባቢ የእስልምና እምነት ብቅ አለ ሆኖም ኢትዮጵያን ሊደፍር አልቻለም።
2. የግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
የግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የተመሠረተችው በመጀመሪያው ምእት ዓመት በዘመነ ሐዋርያት ነው። መስራችዋም ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ የሁለተኛው ወንጌል ፀሐፊ ቅዱስ ማርቆስ ነው።በእስክንድርያ በቅዱስ ማርቆስ ወንጌላዊ የተመሰረተች መሆኗን አውሳብዮስ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ አባት አረጋግጧል። (Eusebius IIE.II.16)እስክንድርያ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከፍ ብለው ከታዩት ከአንጾክያና ከሮም መንበረ ሊቀ ጵጵስና ጋር ዕሪና ያላት ከፍተኛ ቤተ ክርስቲያን ናት።የግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዘመነ ዲዮቅልጥያኖስ ከፍተኛ ፈተናና ስደት ደርሶባታል። በሦስተኛው መቶ ዓመት የምንኩስና ሥርዓት በቅዱስ እንጦንስና በሌሎችም አበው በግብፅ ተጀመረ። ገዳማት ተመሠረቱ በምድረ ግብጽ የተጀመረው ክርስቲያናዊ የምንኩስና ሥርዓት ክርስትናን በተቀበሉ ክፍላተ ዓለም ሁሉ ተስፋፋ።የግብጽ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ከካቶሊክና ከሌሎች የምስራቅ አብያተ ክርስቲያን የተለየችው በ451 ዓ.ም በተደረገው የኬልቄዶን ጉባኤ ሲሆን በዚያን ጊዜ መሪዋ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ሊቀ ጳጳሳት ዘእስክንድርያ ነበር። ቅብጦች በ616 በፋርስ ሃይል ስር ወድቀው እንደነበር ታሪክ ያረጋግጣል። በ642 በአረቦች ተወረሩ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የእስልምና ሃይማኖት የበላይ ሆኖ በክርስቲያኖች ላይ ታላቅ ችግር ደርሳባቸዋል። በተለይ ካልፍ አል ሐኪም በተባለው እስላማዊ መሪ ከ996-1021ከፍተኛ መከራና ችግር ደርሶባቸዋል። 3,000 አብያተ ክርስቲያንን አፍርሶባቸዋል። የግብጽ ክርስቲያኖች ትክክለኛውን ነፃነት ያገኙት እንግሊዞች ግብፅን የቅኝ ግዛት ባደረጉበት የቴሌስ ከቢርን ጦርነት በአስከተለው በ1882 ወቅት ነበር።
3. የሶርያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
የሶርያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን በሚባል የታወቀች ነበረች። ነገር ግን በኬሌቄዶን ጉባኤ ጊዜ የጉባኤውን ውሳኔ ባለመቀበሏ የግብፅን የኢትዮጵያንና የአርመንን አብያተ ክርስቲያን ፈለገ ሃይማኖት በመከተሏ የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ከሁለት ተከፍላለች። የስም አጠራሩም የተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሆኖ መሪዎቿና ምዕመናኑ ያዕቆባዊያን በመባል በመሪያቸው ይጠራሉ።
4. የአርመን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
የአርመን ሕዝብ ክርስትና በመቀበል የመጀመሪያዎቹ ከሆኑት ውስጥ አንዱ ነው። የክርስትና ሃይማኖትን በአርመን ያስፋፋው ትሪዳትስ ሦስተኛ ተብሎ የሚጠራውን የአርመን ንጉሥ ያጠመቀው የቂሳርያና የቀጰዶቅያ መትሮፖሊት የጵጵስና ማዕረግን በ294 ዓ.ም የሾመው ጎርጎርዮስ ከሣቴ ብርሃን ነበር።
ብፁዕ ጎርጎርዮስ የመጀመሪያውንና አሁንም ያለውን መንበረ ሊቀ ጵጵስና በአራራት ተራራ በስተ ሰሜን በኩል በሚገኘው በኢቸሚአዝን አቋቋሙ።በ390 ዓ;ም እንደ አውሮፓ ዘመን አቆጣጠር አርመን በቢዛንታይንና በፋርስ መንግሥት ከሁለት ተከፍላ ነበር። በ430 ዓ’ም የንጉሳቸው ሃይል ተደምስሶ በፋርሳዊያን በአረቦች በቱርኮችና በሩስያዊያን እጅ ወደቀች፤ ተከፋፈለች። ይሁን እንጂ ዘራቸውን ቛንቛቸውን ሥነ ጽሑፋቸውንና ሃይማኖታቸውን በጥንቃቄ ጠብቀው ፈተናውን በመታገስ ኖረዋል።
5. የህንድ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
የቅዱስ ቶማስ ክርስቲያኖች በመባል የሚታወቁት የህንድ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የክርስትና ሃይማኖት በዘመነ ሐዋርያት ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት በአንዱ በቅዱስ ቶማስ አማካይነት የተጀመረ መሆኑ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የታወቀ ነው። ቅዱስ ቶማስ በሕንድ የክርስትና ሃይማኖትን ሲያስፋፋ በሰማዕትነት ሕይወቱን ሰጥቷል።እንዲህ ለመሆኑ በሰባተኛው ምእት ዓመት የተገኘው በመስቀል ላይ የተቀረጸው ቃል ማስረጃ መሆኑ ተጽፏል።ከመሰረቱ ከምሥራቃዊት ሶርያ የመጀመሪያዎቹ የክርስትና እምነት ተከታዮች ወደ ሕንድ ሄደው እንደነበርና የክርስትና ሃይማኖት መስፋፋት እንደቻለም ይተረካል። ጳጳስ የሚላክላቸው ከሶሪያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ነበር።በአሁኑ ጊዜ ግን የራሳቸው ፓትርያርክ ካቶሊክ (አንተ ላዕለ ኩሉ) በሚል የክብር ቅጽል የሚጠራ አላቸው። ይሁን እንጂ የሶርያን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፕትርክና የበላይነት በአክብሮት አንፃር ይቀበላሉ።
እነዚህ አምስቱ የኦርየንታል የምስራቅ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባህርይ አንድ ባህርይ ሆኖ በተዋህዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም ዘእንበለ ዘርአ ብእሲ ተወልዶ ያዳነን መሆኑን በአንድነት ያምናሉ። ስለ መንፈስ ቅዱስም ዘሠረጸ እምአብ በማለት አንድ ናቸው።ሰባቱን ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን ሁሉም ይቀበላሉ። በጸሎተ ቅዳሴ ሊተባበሩ የጌታን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም አብረው ሊቀበሉና ሊያቀብሉ ይችላሉ። ከቋንቋና ካንዳንድ ባህላዊ አመራር በስተቀር ልዩነት የላቸውም።ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በሁሉ ነገር አንድ ስለሆኑ እንደ አንድ ቤተክርቲያን ሊወሰዱ ይችላሉ።
ምንጭ፡ አዲስ መረጃ