Skip to content Skip to sidebar Skip to footer

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ጾም

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ጾም

ጾም ማለት ሰውነት ከሚፈልጋቸው ነገሮች፣ ከጥሉላት ማለትም የእንስሳት ተዋፅኦ ከሆኑ ምግቦች፣ ከማንኛውም
ዓይነት ምግብ ለተወሰነ ጊዜ መከልከል ማለት ነው፡፡ (ፍትሐ ነገሥት፣ ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 15፣ ማቴ.6፥16)፡፡
በጥቅሉ ጾም ሥጋዊው ሰውነት የሚያምረውን፣ የሚያስጎመጀውን ነገር ሁሉ መተው ነው፡፡

የጾም ዓላማው ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ማስገዛት፣ በደልን ለማስተስረይና የነፍስ ዋጋን ለማግኘት ነው፡፡
ጾም ከሃይማኖት ጋራ ግንኙነት አለው፡፡ በተለይም በብሉይ ኪዳን ጾም በአይሁድ ሕዝብ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ
ነበረው፡፡ የብሉይ ኪዳን ነቢያት ከእግዚአብሔር ጋር ለመነጋገር በፈለጉ ቁጥር ምግብ አይበሉም፣ ውሃም አይጠጡም፡፡
(ዘጸ.34፥ 28) በኃጢአት ምክንያት የሚመጣውን የእግዚአብሔርን ቁጣ በጸሎት እና በጾም ማስቀረት ይቻላል፡፡
(ዮና.3፥7-10፤ ኢዩ.2፥15)፡፡ በአዲስ ኪዳንም ጾም ሰው ሠራሽ(በሰው የተሰጠ) ሕግ አይደለም፡፡

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው የመሲሐዊ አገልግሎቱ መጀመሪያ አድርጎታል፡፡ (ማቴ.4፥2፣ ሉቃ.4፥2)፡፡ ጾም ርኩሳን መናፍስትን የማራቅ ኃይል እንዳለው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሯል (ማቴ.17፥21፣ ማር.9፥2)፡፡ ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ የታዘዙት ሐዋርያትም ከመንፈስ ቅዱስ በየጊዜው ትእዛዝ የሚቀበሉት በጸሎት እና በጾም ወቅት ነበር፡፡ (የሐዋ.ሥራ 13፥2)፡፡የወንጌል ሰባኪ ሆነው የሚያገለግሉ ዲያቆናትና ቀሳውስት የሚሾሙትም በጾምና በጸሎት ነው፡፡ (የሐዋ.ሥራ 13፥3፣14፥23)፡፡ደጋግ ሰዎች(ጻድቃን) የሚፈልጉትን ያገኙት በጾምና በጸሎት እግዚአብሔርን ማልደው ነው፡፡ (ዕዝራ. 8፥21፣ ነህ.9፥1-3፣አስ.4፥16-17፤ የሐዋ.ሥራ 10፥30፣ 13፥2-3)፡፡

የጾም ሃይማኖታዊ ትርጓሜው ጾም እግዚአብሔርን መለመኛ እና የኃጢአት ማስተስረያ ስለሆነ ሥጋዊ ምኞትን ከሚቀሰቅሱ የእንስሳት ተዋጽኦ እና ከአልኮል መጠጦች መራቅ ግዴታ ነው፡፡(ዳን.10፥2-3)፡፡ጾም በሐዋርያትና በሊቃውንትም ዘንድ ሲሰበክ ኖሯል፡፡(ፍትሐ ነገሥት፣ ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 15፣ዲድስቅልያ አንቀጽ 29)፡፡ “ነዳያንን ለመመገብ የሚጾም ንዑድ
ክቡር ነው” እንደተባለ ጾመኛው ለምሳው ወይም ለራቱ ያሰበውን ወጭ ነዳያያን እንዲረዳበት ለድኩማን ድርጅት ወይም በቤተ ክርስቲያን አካባቢ ለሚገኙ ነዳያን መስጠት ጾሙን የበለጠ ፍጹም ያደርገዋል፡፡ (ኢሳ.58፥6-11)፡፡

ጾም ከምግብ መራቅ ብቻ ሳይሆን ዐይን ክፉ ከማየት፣አንደበት ክፉ ከመናገር፣ ጆሮም ክፉ ከመስማት የተቆጠበ እንደሆነ ጾሙ እውነተኛ ጾም ይሆናል፡፡ (ማቴ.5፥21-30፤ ቅዱስያሬድ ጾመ ድጓ)፡፡የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የራስዋ የሆነ የጾም ሕግና ሥርዐት አላት፡፡በሕጓም መሠረት ሰባት የአጽዋት ጊዜያት አሏት፤ እያንዳንዳቸው የራሳቸው ሕግና የጾም ሥርዓት አላቸው፡፡
1ኛ. ዐቢይ ጾም
2ኛ. ረቡዕና ዓርብ
3ኛ. ነነዌ
4ኛ. ገሃድ
5ኛ.ጾመ ነቢያት
6ኛ. ጾመ ሐዋርያት
7ኛ. ጾመ ፍልሰታ ለማርያም

1. ዐቢይ ጾም

ዐቢይ ጾም ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ ለአርባ ቀንና ሌሊት የጾመው ጾም ነው፡፡ (ማቴ.4፥1) የጌታችንን ምሳሌ በመከተል ቤተክርስቲያን ይህንን ጾም ትጾማለች፡፡

ዐቢይ ጾም (ታላቁ ጾም) ስምንት ሳምንታት ሲሆን 55 ቀናት አሉት፡፡የመጀመሪያው ሳምንት ጾመ ሕርቃል ይባላል፡፡ ሕርቃል(ኢራቅልዮስ) የቤዛንታይን ንጉሥ ነበር (614 ዓ.ም)፡፡ይህ ሳምንት በስሙ የተጠራበት ምክንያት እንደሚከተለው ነው፡፡

በዘመኑ ፋርሳውያን ኢየሩሳሌምን ወርረው የጌታን መስቀል ማርከው ወስደው ነበር፡ ሕርቃል ወደ ፋርስ ዘምቶ ፋርሳውያንን ድል ካደረገ በኋላ መስቀሉን ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሷል፡፡ በሕርቃል ድልና በመስቀሉ መመለስ በጣም የተደሰቱት በኢየሩሳሌም የነበሩት ክርስቲያኖች ከዐቢይ ጾም በፊት ያለውን የመጀመሪያውን ሳምንት ለሕርቃል መታሰቢያ እንዲጾም ወስነው በቀኖና ውስጥ አካትተውታል፡፡ቤተ ክርስቲያናችንም በቀኖናዋ አስገብታ ተቀብላዋለች፤ የዐቢይ ጾም አካል እንዲሆንም አድርጋለች፡፡ (ፍትሐ ነገሥት፣ ፍትሕ መንፈሳዊ፣አንቀጽ 15)፡፡

የዐብይ ጾም የመጨረሻ ሳምንት ሰሙነ ሕማማት ይባላል፤ሐዋርያት የክርስቶስን ሕማማት (ነገረ መስቀል) እያሰቡ ጾመዉታል፡፡ ይህም የዐቢይ ጾም አካል ሆኖ ይቆጠራል፡፡ ዐቢይ ጾም የመባሉ ምክንያት በመጀመሪያ የጌታ ጾም ስለሆነ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ፣ በዚህ ጾም የሰይጣን ፈተናዎች(የገንዘብ ፍቅር፣ ስግብግብነት እና እብሪተኝነት) ድል የተነሱበትና የሚነሱበት ስለሆነ ነው፡፡ሁሉም ክርስቲያኖች ወጣትም ሆኑ ሽማግሌዎች የጌታን ጾም መጾም አለባቸው፡፡

የቤተ ክርስቲያናችንን መዝሙር ንባቡን ከዜማው አስማምቶ የጻፈው ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓ መጽሐፉ ውስጥ በዐቢይ ጾም ለሚገኙት እሑዶች (ሳምንታት) የተለየ መዝሙር ስለሠራላቸው እያንዳንዱ እሑድ (ሳምንት) በመዝሙሩ ስም ይጠራል፡፡

የመጀመሪያው እሑድ (ሳምንት) ዘወረደ ይባላል፤ ዘወረደ ማለት ከላይ የወረደው ማለት ነው፡፡በመዝሙር መጽሐፉ
መጀመሪያ ላይ አምላከ ከሰማይ መውረዱን፣ ሰው መሆኑንና መሰቀሉን ስለሚያወሳ ነው፡፡ (ዮሐ.3፥13)፡፡

ሁለተኛው እሑድ (ሳምንት) ቅድስት ይባላል፤ ስለ ዕለተ እሑድ ቅድስና ስለሚያወሳ ነው፡፡

ሦስተኛው እሑድ (ሳምንት) ምኵራብ ይባላል፤ ጌታ በመዋዕለ ስብከቱ ወደ ምኵራብ ገብቶ ማስተማሩን ስለሚያወሳ ነው፡፡

አራተኛው እሑድ (ሳምንት) መጻጉዕ ይባላል፤ ጌታ ድውያንን መፈወሱን፣ ዕውራንን ማብራቱን የሚያነሣ መዝሙር
ስለመሚዘመርበት ነው፡፡ (ዮሐ.5፥1-9)

አምስተኛው እሑድ (ሳምንት) ደብረ ዘይት ይባላል፤ ደብረዘይት የግእዝ ቃል ሲሆን የዘይት ተራራ ማለት ነው፡፡ ጌታችን
በደብረ ዘይት ሆኖ ያስተማረውን የዳግም ምጽአት ነገር ስለሚያወሳ ነው፡፡

ስድስተኛው እሑድ (ሳምንት) ገብር ኄር ይባላል፤ ገበር ኄር ማለት ታማኝ አገልጋይ ማለት ነው፡፡የጌታውን አምስት መክሊት
ተቀብሎ አምስት ተጨማሪ መክሊትን ያተረፈው ታማኝ አገልጋይ ታሪክ ስለሚነገርበት ነው፡፡ (ማቴ.25፥14-30)፡፡

ሰባተኛው እሑድ (ሳምንት) ኒቆዲሞስ ይባላል፤ በሌሊት ወደ ጌታችን እየመጣ ይማር የነበረውን የኒቆዲሞስን ታሪክ
የሚዘክር መዝሙር ስለሚዘመርበት ነው፡፡

ስምንተኛው እሑድ (ሳምንት) ሆሣዕና ይባላል፤ ጌታ ሆሣዕና በአርያም እየተባለ ወደ ቤተመቅደስ የገባበት ዕለት መታሰቢያ ስለሆነ ነው፡፡ ከሠርከ ሆሣዕና እስከ ትንሣኤ ያለው ሳምንት “ሰሙነ ሕማማት” ይባላል፡፡ በነዚህ ቀናት ብዙ የምግብ ዓይነቶች አይበሉም፡፡ ስግደት ይሰገዳል፡፡የጌታን መከራና ሞት የሚያስታውሱ ምንባባት ከቅዱሳት መጻሕፍትና ከድርሳናት ተውጣጥተው በ“ግብረ ሕማማት” ይነበባሉ፡፡አዳም ከፈጣሪው ተጣልቶ የኖረውን የጨለማው የመከራ ዘመን በማስታወስ መንበረ ታቦቱ በጥቁር ልብስ ይሸፈናል፡፡ ልብሰ ተክህኖውም ጥቁር ነው፡፡ይህ ሳምንት የ5500 ዘመን ዓመተ ፍዳና ዓመተ ኩነኔ የሚዘከርበት በመሆኑ ጸሎተ ፍትሐት እና ጸሎተ አስተስርዮ አይፈጸምም፡፡ ጸሎተ ፍትሐት እና ጸሎተ አስተስርዮ የሚደረገው የሆሣዕና ዕለት ነው፡፡

ጸሎተ ሐሙስ

ጸሎተ ሐሙስ ጌታ በፍጹም ትሕትና ደቀ መዛሙርቱን ያጠበበትና ግብር ያገባበት፣ ምሥጢረ ቁርባንን ያሳየበት ዕለት ነው፡፡ በዚህ ዕለት ቅዳሴ ይቀደሳል፡፡ከቅዳሴው በፊት ካህኑ ውኃውን በብርት አድርጎ የምእመናንን እግር ያጥባል፡፡ጸሎተ ቅዳሴውም ከተፈጸመ በኋላ ምእመናኑ ወደ የቤታቸው ይሄዳሉ፡፡

ከጸሎተ ሐሙስ፣ በበነጋው ዐርብ የስቅለቱ መታሰቢያ ዕለትሥዕለ ስቅለት ተሠርቶ ለስቅለቱ ነክ የሆኑ ከቅዱሳትመጻሕፍትና ከሌሎች ሃይማኖታዊ መጻሕፍት ምንባቦች ሲነበቡ ይዋላል፡፡ሠርክ ሲሆን እያንዳንዱ ምእመን ወደ ቄሱ እየቀረበ በወይራ ቅጠል ይጠበጠባል፡፡ ይህም በወይራ ቅጠል መጠብጠብ የጌታ ግርፋት ምሳሌ ነው፡፡ ቀጥሎም አራት መቶ እግዚኦታ ይደርሳል፡፡ ለበዓሉ የተሠሩ መዝሙራትና ምንባባት ከተደረሱ በኋላ ንሴብሖ ለእግዚአብሔር ተብሎ መስቀል ከማሳለም በቀር ኑዛዜ ተደርጎ እግዚአብሔር ይፍታ ይባላል፡፡ጸሎተ አስተሥርዮ ይደረጋል። (ፍትሐ ነገሥት፣ ፍትሕ መንፈሳዊአንቀጽ15)፡፡

በአሥራ ሁለት ሰዓት ሠርሖተ ሕዝብ ይሆናል፡፡ሐዋርያት የጌታን ትንሣኤ ሳናይ እህል ውሃ አንቀምስም ብለው እስከትንሣኤ አክፍለዋል፡፡
በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስቲያኖች ለሁለት ቀናት ከማንኛውም ዓይነት
ምግብ ለመታቀብ የሚችሉ አርብ እና ቅዳሜን ያልቻሉ ደግሞ ቅዳሜ ብቻ እንዲጾሙ (እንዲያከፍሉ) ታዟል። (ሉቃ.5፥33-35፣ ፍትሐ ነገሥት፣ ፍትሕ መንፈሳዊ፣ አንቀጽ 15 ቁ. 578)

ቅዳሜ ጠዋት ምእመናኑና ካህናቱ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ይሰበሰባሉ፤ የጠዋት ጸሎት ካለቀ በኋላ “ገብረ ሰላመ በመስቀሉ” ክርስቶስ በመስቀሉ ሰላምን አደረገ። የመሥራች እየተባለ በቤተ ክርስቲያን ለተሰበሰበው ሁሉ ቄጤማ ተባርኮ ይሰጣል፤ የምሥራች ምልክት ነውና፡፡ ምእመናን በራሳቸው ያስሩታል፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን ላልመጡትም ካህናት ልብሰ ተክህኖ ለብሰው መስቀልና ቃጭል ይዘው ቄጤማውን የምሥራች እያሉ ያድላሉ፡፡

የቀድሞዋ ሰንበት (ቅዳሜ) እግዚአብሔር ፍጥረታትን ሁሉ ከፈጠረ በኋላ ከሥራው ያረፈበት ዕለት እንደሆነ ይህ ደግሞ የማዳን ሥራውን በመስቀል ላይ ፈጽሞ በመቃብር ተኝቶ ያለፈበት ዕለት ነው፡፡ይህ ዕለት “ስዑር ቀዳም” ይባላል፡፡ ስዑር መባሉም በዓመት አንድ ጊዜ ስለሚጾም ነው፡፡በተጨማሪም ”ለምለም ቅዳሜ” ተብሎም ይጠራል፤ በዚህ ቀን ቄጤማ
ይታደላልና ቄጤማውም የምሥራች ምልክት መሆኑ ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን ምድር በጥፋት ውሃ ስትሸፈን እና የኖኅ መርከብ ማረፊያ አጥታ ስትንሳፈፍ የውሃውን ሁኔታ ለመረዳት ኖኅ ርግብን በመርከቡ መስኮት አሾልኮ ላካት፡፡እሷም የወይራ ቅጠል ባፏ ይዛለት ተመለሰች፡፡ ኖኅ በዚህ የወይራ ቅጠል የውሃውን መድረቅ ተረድቶ ተመለሰ፡፡መርከቡንም ለማሳረፍ ተዘጋጀ፡፡የወይራው ቅጠል ለጥፋት ውሃ መድረቅ የምሥራች መንገሪያ እንደሆነ ሁሉ አሁንም በክርስቶስ ሞት ጥፋት፣ኃጢአትና ሞት ከሰው ልጆች ተወገደ እያለች ቤተ ክርስቲያን ለምእመናን ቄጤማ ታድላለች፡፡ (1ጴጥ.3፥19-21)

2. የረቡዕ እና ዓርብ ጾም

በየሳምንቱ ረቡዕ እና ዓርብ ከትንሳኤ ጀምሮ እስከ ጰራቅሊጦስ እሑድ ድረስ ከሚገኙና እንዲሁም ልደትና ጥምቀት
ከሚውሉባቸው ረቡዕ እና ዓርብ በቀር ዓመቱን ሙሉ ይጾማሉ፡፡የሚጾሙበትም ምክንያት አላቸው፡፡ረቡዕ የአይሁድ ሸንጎ ጌታን ዓርብ ዕለት ለመስቀል ምክረ ሞቱን የፈጸሙበት ዕለት ነው፡፡(ዮሐ.11፥46-53) መድኃኔዓለም ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሲል ተወሰነበትን የሞት ውሳኔ ሁልጊዜ በማስታወስ ክርስቲያኖች እንዲጾሙ መመሪያ ተሰጥቷል፡፡

ዓርብ እንደሚታወቀው ጌታ የተሰቀለበት በሥጋ የሞተበት ብዙ ዘመን ሲጠበቅ ነበረው ተስፋ የተፈጸመበት ቅዱስ ዕለት ነው፡፡(ዮሐ.19፥17-30፣ ሉቃ.23፥26-49) ስለሆነም ልደትና ጥምቀት ከሚውሉባቸው እንዲሁም በበዓለ ሃምሳ ውስጥ ካሉት ረቡዕ እና ዓርብ በቀር በየሳምንቱ በጾምና በጸሎት እንዲከበሩ በቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና ታዝዟል፡፡ (ፍትሐ ነገሥት፣ ፍትሕመንፈሳዊ አንቀጽ 15፤ ዲድስቅ 29)

3. የነነዌ ጾም

ይህ ጾም የሦስት ቀን ጾም ነው፡፡ ሰኞ፣ ማክሰኞ እና ረቡዕ፡፡ ይህ ጾም አንድ ጊዜ በጥር አንድ ጊዜ በየካቲት ወር ይሆናል፡፡የቤተ ክርስቲያን አባቶች ይህን ጾም የወሰኑት የነነዌ ሰዎች በጾምና በጸሎት ከዚህ የጾም ዘመን በስተጀርባ ያለው ምክንያት የነነዌ ሰዎች በጸሎትና በጾም ከእግዚአብሔር ቁጣ እንደዳኑ ለመግለጽ ነው፡፡ምእመናን በዚህ ጾም ምሕረትንና በረከቶችን ይቀበላሉ፡፡ (ዮና.3፥ 5-9፤ ማቴ.12፥39)

4. ገሃድ

ይህ ጾም በልደት እና በጥምቀት ዋዜማ ይጾማል፡፡ልደት እና ጥምቀት ረቡዕና ዓርብ ሲውሉ በሌሊት ስለሚቀደስና ስለሚበላ በለውጡ በዋዜማው ሐሙስና ማክሰኞ ይጾማል፡፡ (ፍትሐነገሥት፣ ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 15) ይህም ጾም በየዓመቱ እንዲጾም በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ተወስኗል፡፡

5. የነቢያት ጾም

የጾሙ ጊዜ ከሕዳር 15 እስከ ታኅሣሥ 28 ቀን ያለው ነው፡፡ይህን ጾም የምንጾመው ነቢያት በየዘመናቸው ስለ ክርስቶስ መምጣት በናፍቆት ይጾሙና ይጸልዩ ስለነበር የእነርሱን አርአያ ተከትለን የክርስቶስን ልደት ከማክበራችን ቀደም ብለን ይህን ጾም እንድንጾም በሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ተሠርቷል፡፡ (ፍትሐ ነገሥት፣ ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 15)

6. የሐዋርያት ጾም

ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ለስብከተ ወንጌል ከመሔዳቸው በፊት የጾሙት ነው፡:፡ምእመናንም እነርሱን ምሳሌ አድርገው ከጰራቅሊጦስ እሑድ ማግስት ጀምረው እንዲጾሙ ቤተ ክርስቲያናችን ታዛለች፡፡የሐዋርያት ጾም ከትንሣኤ ከሃምሳ ቀናት በኋላ ስለሚመጣ አንዳንድ ጊዜ ከአርባ ቀናት ይበልጣል፤ አንዳንድ ጊዜም ከሠላሳ ቀን ያንሳል፡፡

7. የፍልሰታ ጾም

የፍልሰታ ጾም ከነሐሴ 1 እስከ 15 ቀን ያለው ነው፡፡እመቤታችን ያረፈችው በጥር 21 ቀን 50 ዓ.ም ነው፡፡ሐዋርያት ሊቀብሩ ወደ ጌቴሴማኒ ይዘዋት ሲሔዱ አይሁድ በታተኗቸው፡፡በዚህ ጊዜ መላእክት የእመቤታችንን ሥጋዋን ወስደው በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አኑረውታል፡፡ (ተአምረ ማርያም፣ ስንክሳር ነሐሴ 16 ቀን)፡፡ሐዋርያው ዮሐንስ በተመስጦ እየሄደ ሥጋዋን ያጥን ነበር፡፡ለሐዋርያት ይህን ይነግራቸዋል፡፡ለዮሐንስ ተገልጣ ለእኛ ሳትገለጥ ብለው ሱባዔ ገቡ፡፡ሁለተኛው ሱባኤ ሲፈጸም በ14ኛው ቀን መልአክ ሥጋዋን አምጥቶ ሰጥቶአቸው ቀብረዋታል፡፡ በሦስተኛው ቀን ነሐሴ 16 ቀን ተነሥታ አርጋለች፡፡ (ተአምረ ማርያም፣ ስንክሳር ነሐሴ 16 ቀን)፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን የእመቤታችንን በረከት ለማግኘት ትጾማለች፡፡በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ይህን ጾም ሕፃናቱ ሳይቀሩ ይጾሙታል፡፡በዚህ የአሥራ አምስት ቀን ጊዜ ውስጥ የማይጾምና የማይቆርብ ሕፃን የለም፡፡ብዙ ሰዎች ቤታቸውን እየተዉ ሱባዔ እየገቡ ከላመ ከጣመ ምግብ በመከልከል ጥሬ እየቆረጠሙ ውሃ እየጠጡ በጾምና በጸሎት ይሰነብታሉ፡፡ በፍልሰታ ጾም በጠቅላላ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያለው ሁኔታ ሕዝቡ ልጅ አዋቂ ሳይል የሚያሳየው ሃይማኖታዊ ሥርዐት ኢትዮጵያ ለእመቤታችን የቃል ኪዳን አገር እንደሆነች ይመሰክራል፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊትና ቀኖና መሠረት ከሰባት ዓመት በላይ የሆኑት ክርስቲያኖች ከላይ የተጠቀሱትን አጽዋማት እንዲጸሙ ታዘዋል፡፡ቅዳሴ የሚቀደሰውም ከቅዳሜና ከእሑድ በቀር በጾም ወራት ሁሉ ነው፡፡

ምንጭ፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንእምነት፣ የአምልኮ ሥርዓት እና የውጭ ግንኙነት