Skip to content Skip to sidebar Skip to footer

ጸሎተ ሃይማኖት

ጸሎተ ሃይማኖት

 

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ሁሉን በያዘ ሰማይንና ምድርን የሚታየውንና የማይታየውን በፈጠረ በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን።

ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ ጋር በነበረ የአብ አንድ ልጅ በሚሆን በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን።

ከብርሃን የተገኘ ብርሃን፤ ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ፤ የተፈጠረ ያይደለ የተወለደ፤ በመለኮቱ ከአብ ጋር የሚተካከል።

ሁሉ በእርሱ ሆነ ያለ እርሱ ምንም ምን የሆነ የለም፤በሰማይም ያለ በምድርም ያለ።

ስለ እኛ ስለ ሰዎች ስለመዳናችን ከሰማይ ወረደ። በመንፈስ ቅዱስ ግብር ከቅድስት ድንግል ማርያም ፈጽሞ ሰው ሆነ።

ሰው ሆኖ በጰንጤናዊው በጲላጦስ ዘመን ስለእኛ ተሰቀለ፤ታመመ፤ ሞተ፤ ተቀበረ፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተጻፈ።

በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ።ዳግመኛም ሕያዋንንና ሙታንንም ይገዛ ዘንድ በጌትነት ይመጣል። ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።

ጌታ ማኅየዊ በሚሆን ከአብ በሰረፀ በመንፈስ ቅዱስም እናምናለን፤ እንሰግድለት እናመሰግነውም ዘንድ ከአብና ከወልድ ጋር በነቢያት የተናገረ።

ከሁሉ በላይ በምትሆን ሐዋርያት በሰበሰብዋት በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን።

ኃጢአትን ለማስተሥረይ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን።

የሙታንንም መነሣት ተስፋ እናደርጋለን።

የሚመጣውንም ሕይወት ለዘለዓለሙ አሜን።

ጸሎተ ሃይማኖትን ከነትርጉሙ ጠንቅቆ ማወቅ ሃይማኖትን በተገቢው መንገድ መረዳት መቻል ማለት ነው። ስለዚህም እያንዳንዳችን ስለ ሃይማኖታችን ብንጠየቅ የጸሎተ ሃይማኖትን ትርጉም ጠንቅቀን ካወቅን ማንነታችንን በሚገባ መግለጽ እንችላለን። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ የሆነ ምእመን ሁሉ እንደ አባታችን ሆይ እና እንደ እመቤታችን ጸሎት በቃሉ ጸሎተ ሃይማኖትን ማወቅ ይጠበቅበታል።

ሁሉን በያዘ ሰማይንና ምድርን የሚታየውንና የማይታየውን በፈጠረ በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር  አብ እናምናለን።

ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አንድ አምላክ ስለሆነ እግዚአብሔርና ስለ ፍጥረቱ ይናገራሉ፦

  • እግዚአብሔር በስድስት ቀን ሰማይንና ምድርን፥ ባሕርንም፥ ያለባቸውንም ሁሉ ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን ዐርፎአልና።ዘጸ.፳፡፲፩  አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው፤ ዘዳ.፮፡፬
  • ዓይናችሁን ወደ ላይ አንሥታችሁ ተመልከቱ፤ እነዚህን የፈጠረ ማን ነው? ሠራዊታቸውን በቍጥር የሚያወጣ እርሱ ነው… በኃይሉ ብዛትና በችሎቱ ብርታት አንድስ እንኳ አይታጣውም። ኢሳ.፵፤፳፮
  • እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከእኔ ሌላም የሚያድን የለም። ኢሳ.፵፬፡፲፩
  • እኔ እግዚአብሔር ነኝ ከእኔም ሌላ ማንም የለም፤ ከእኔም በቀር አምላክ የለም፤ በፀሐይ መውጫና በምዕራብ
    ያሉ ከእኔ በቀር ሌላ እንደሌለ ያውቁ ዘንድ አስታጠቅሁህ ግን አላወቅኸኝም፤ ኢሳ.፵፭፡፲፰
  • ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን፥ ፩ ቆሮ.፰፡፮
  • ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ። ኤፌ.፬፡፮

 

ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ ጋር በነበረ የአብ አንድ ልጅ በሚሆን በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን።

ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ስለ አብ አንድ ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ይናገራሉ፦

  • በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ
    ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዮሐ.፫፡፲፮
  • በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ አሉት። ሐዋ.፲፮፡፴፩
  • እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን። ፩ ቆሮ.፰፡፮
  • ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥ መላስም ሁሉ
    ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው። ፊል.፪፡፲-፲፩
  • አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ፥ ደግሞም። እኔ አባት እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል። ዕብ.፩፡፭
  • ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ… ይህ ተጽፎአል። ዮሐ.፳፡፴፩
  • አባት ሆይ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ። ዮሐ.፲፯፤፭ ፫

 

ከብርሃን የተገኘ ብርሃን፤ ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ፤ የተፈጠረ ያይደለ የተወለደ፤  በመለኮቱ ከአብ ጋር የሚተካከል።

ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ከብዙ በጥቂቱ የአብና የወልድን እኩል መሆን ይናገራሉ፦

  • በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ዮሐ.፩፡፩
  • እኔና አብ አንድ ነን። ዮሐ.፲፡፴፤
  • እኔን ያየ አብን አይቶአል። ዮሐ.፲፬፡፱
  • ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው። ዮሐ.፲፮፡፲፭
  • ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ደግሞ ዓለምን እተወዋለሁ ወደ አብም እሄዳለሁ። ዮሐ.፲፮፡፳፰
  • ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ
    ነው። ዮሐ.፫፡፲፱

 

ሁሉ በእርሱ ሆነ ያለ እርሱ ምንም ምን የሆነ የለም፤ በሰማይም ያለ በምድርም ያለ።

ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ከብዙ በጥቂቱ ሁሉም ነገር በወልድ እንደሆነ ይናገራሉ፦

  • ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም። ዮሐ.፩፡፫
  • እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው። የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም
    አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር
    ነው። ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል። ቆላ.፩፡፲፮

ስለ እኛ ስለ ሰዎች ስለመዳናችን ከሰማይ ወረደ። በመንፈስ ቅዱስ ግብር ከቅድስት ድንግል ማርያም ፈጽሞ ሰው ሆነ።

ከዚህ በታች ያሉት ጥቅሶች ከሰማይ መውረዱንና ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱን ይናገራሉ፦

  • እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።ኢሳ.፯፡፲፬
  • እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች። ማቴ.፩፡፲፰
  • የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤ ገላ.፬፡፬

 

ሰው ሆኖ በጰንጤናዊው በጲላጦስ ዘመን ስለእኛ ተሰቀለ፤ ታመመ፤ ሞተ፤ ተቀበረ፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተጻፈ።

ከዚህ በታች ያሉት የተዘረዘሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የወልድን ሕማሙን፣ ሞቱንና ትንሣኤውን ይናገራሉ፦

  • ጲላጦስም ሁከት እንዲጀመር እንጂ አንዳች እንዳይረባ ባየ ጊዜ፥ ውኃ አንሥቶ። እኔ ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም
    ንጹሕ ነኝ፤ እናንተ ተጠንቀቁ ሲል በሕዝቡ ፊት እጁን ታጠበ። ማቴ.፳፯፡፳፬
  • በዚያን ጊዜ በርባንን ፈታላቸው፥ ኢየሱስን ግን ገርፎ ሊሰቀል አሳልፎ ሰጠ። ማቴ.፳፯፡፳፮
  • ኢየሱስም ሁለተኛ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ነፍሱን ተወ።
  • ጲላጦስም እንዲሰጡት አዘዘ። ዮሴፍም ሥጋውን ይዞ በንጹሕ በፍታ ከፈነው፥ ከዓለት በወቀረው በአዲሱ

መቃብርም አኖረው፥ በመቃብሩም ደጃፍ ታላቅ ድንጋይ አንከባሎ ሄደ። ማቴ.፳፯፡፶፱

  • እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፤ የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ። ማቴ.፳፰፡፮
  • ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም። ሉቃ.፳፬፡፭
  • አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል። ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ ትንሣኤ
    ሙታን በሰው በኩል ሆኖአልና። ፩ቆሮ.፲፭፡፳-፳፩

 

በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ። ዳግመኛም ሕያዋንንና ሙታንን ይገዛ ዘንድ በጌትነት ይመጣል። ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።

ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የወልድን ዕርገቱን እና ዳግም መምጣቱን ይናገራሉ፦

  • ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ ወደ ሰማይም ዐረገ። ሉቃ.፳፬፡፶፩
  • በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም። ሉቃ.፩፡፴፫
  • ከሰማይ ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው። ዮሐ.፫፡፲፫
  • ይህንም ከተናገረ በኋላ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው። ሐዋ.፩፡፱
  • ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ አለ። ሐዋ.፯፡፶፮• የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር
    በአባቱ ክብር ይመጣል፤ለሁሉ እንደ ሥራው ያስረክበዋል። ማቴ.፲፮፡፳፯
  • ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም
    የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ። ፩ተሰ. ፬፡፲፮

ጌታ ማኅየዊ በሚሆን ከአብ በሰረፀ በመንፈስ ቅዱስም እናምናለን፤ እንሰግድለት እናመሰግነውም ዘንድ ከአብና ከወልድ ጋር በነቢያት የተናገረ።

ከዚህ በታች ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ስለ መንፈስ ቅዱስና ለመንፈስ ቅዱስ የሚገባውን ክብር ይናገራሉ፦

  • እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ
    እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ከእናንተ
    ጋር ነኝ። ማቴ.፳፰፡፲፱-፳
  • እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ
    ይመሰክራል። ዮሐ.፲፭፡፳፮
  • ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ
    ተነድተው ተናገሩ። ፪ጴጥ.፩፡፳፩
  • መንፈስም እውነት ነውና የሚመሰክረው መንፈስ ነው። የሚመሰክሩት መንፈሱና ውኃው ደሙም ሦስት
    ናቸውና፤ ሦስቱም በአንድ ይስማማሉ። ፩ዮሐ.፭፡፰

 

ከሁሉ በላይ በምትሆን ሐዋርያት በሰበሰብዋት በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን።

ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይናገራሉ፦

  • አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም። ማቴ.፲፮፡፲፰
  • ባሎች ሆይ፥ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ። ኤፌ.፭፡፳፭
  • …እነርሱንም ባይሰማ፥ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ደግሞም ቤተ ክርስቲያንን ባይሰማት፥ እንደ አረመኔና እንደ
    ቀራጭ ይሁንልህ። ማቴ.፲፰፡፲፯

 

ኃጢአትን ለማስተሥረይ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን።

ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ስለ ጥምቀት ይናገራሉ፦

  • ያመነ የተጠመቀም ይድናል፥ ያላመነ ግን ይፈረድበታል። ማር.፲፮፡፲፮
  • ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። ከሥጋ የተወለደ
    ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው። ዮሐ.፫፡፭
  • ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ
    ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ። ሐዋ.፪፡፴፰
  • አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤ ኤፌ.፬፡፭

የሙታንንም መነሣት ተስፋ እናደርጋለን።

ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ስለ ትንሣኤ ሙታን ይናገራሉ፦

  • በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉቱ ብዙዎች ይነቃሉ፤ እኵሌቶቹ ወደ ዘላለም ሕይወት፥ እኵሌቶቹም ወደ
    እፍረትና ወደ ዘላለም ጕስቍልና። ዳን.፲፪፡፪• በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤
    መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና። ዮሐ.፭፡፳፱

 

የሚመጣውንም ሕይወት ለዘለዓለሙ አሜን።

ከዚህ በታች ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ስለ ዘላለማዊ ሕይወት ይናገራል፦

  • እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት። ዮሐ.፲፯፡፫