የመካነ ሕይወት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ወርሃዊ የልምድ ልውውጥ ለወጣቶች እየሰጠች ትገኛለች
ቦስተን የሚገኘው የመካነ ሕይወት ቅዱስ ሚካኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወጣቶች
በመንፈሳዊና እና በአለማዊ ህይወታቸው ያላቸውን እውቀት ለማጎልበት የሚያስችል የልምድ ልውውጥ
ከተወሰኑ ወራቶች በፊት የጀመረ ሲሆን በተለያዩ ደረጃ ላይ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቷን ምዕመናን በመጋበዝ
መርሃ ግብሩን እያቀረበ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል። ከጥቂት ወራት በፊት የተጀመረው ይህ ዝግጅት በየወሩ
እሁድ ከቅዳሴ በኋላ በቤተ ክርስቲያኑ የታችኛው ክፍል በመሰጠት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ይህ መርሃ ግብር ስለ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሰረታዊ እና ዝርዝር መረጃዎችን የሚያቀርብ ሲሆን ከዚህ
በተጨማሪ ተጋባዥ እንግዶቹ አንዳንድ ጊዜ በኮሌጅ ቆይታቸው ወቅት መንፈሳዊ ህይወታቸው ምን አይነት
መልክ እንደነበረው እና ያጋጠማቸውን ችግሮች ለታዳሚ ወጣቶቹ እንደሚገልጹ ለመረዳት ተችሏል ። እንግዶቹ
ለወጣቶቹ ካሉባቸው ሁኔታዎች አንጻር ያለፉባቸውን ሌሎች ጠቃሚ ልምዶች የሚያካፍሉ ሲሆን ወጣቶቹም
ተያያዥነት ያላቸውን ጥያቄዎች በመጠየቅ ተጨማሪ መረጃዎችን እንደሚያገኙ ተገልጿል። እስከ አሁን በነበረው
ዝግጅት ብዙ እንግዶች ተጋብዘው ለወጣቶቹ ገንቢ የሆኑ መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ እንደቆዩ ለመረዳት ተችሏል።
በመካነ ህይወት የሰንበት ትምህርት ቤት ማለትም በአንቀጸ ተዋህዶ እየተዘጋጀ የሚቀርበው ይህ መርሃ ግብር ተጠናክሮ
እንዲቀጥል ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው የሚገልጹት ወላጆች ይህ መሰሉ የልምድ ልውውጥ ሰፋ ባለ መልኩ ተጠናክሮ
እንዲቀጥል ሃሳባቸውን ጨምረው ገልጸዋል።ይህንን ዝግጅት በቅርበት ከሚከታተሉ የሰንበት ትምህርት ቤቱ አባላት
ለመረዳት እንደተቻለው ይህ መርሃ ግብር ሁኔታዎች እስከፈቀዱ ድረስ እንደሚቀጥል ተሰፋቸውን ገልጸዋል።
የመካነ ሕይወት ቅዱስ ሚካኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይህንን እና ሌሎች ትምህርታዊ
ዝግጅቶች በማዘጋጀት ልጆቿን በመንከባከብ በመንፈሳዊ እና በአለማዊ ህይወታቸው የተሳካ እንዲሆን እና
በማህበረሰቡ ውስጥ ጠቃሚ ዜጋ እንዲሆኑ የምታደርገው ይበል የሚያሰኝ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ያላትን ጠንካራ
ቁርጠኝነት ያረጋግጣል።